1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የግንቦት 5 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ግንቦት 5 2016

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በዶሀ ዳይመን ሊግ ለድል በቅተዋል ። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቸስተር ሲቲ እና አርሰናል ዘንድሮ ዋንጫውን ለማንሳት አንገት ለአንገት ተናንቀዋል ። በጀርመን ቡንደስሊጋ፦ የዋንጫ ባለድሉ ባዬርን ሌቨርኩሰን አመርቂ ድል እየተደጋጋመ ነው ። ሁለት ተጨማሪ የዋንጫ ግጥሚያዎች ይጠብቁታል ።

https://p.dw.com/p/4fnaS
Tottenham Hotspur Stadium in London
ምስል Shaun Botterill/empics/picture alliance

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በዶሀ ዳይመን ሊግ  ለድል በቅተዋል ። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቸስተር ሲቲ እና አርሰናል ዘንድሮ ዋንጫውን ለማንሳት አንገት ለአንገት ተናንቀዋል ። በጀርመን ቡንደስሊጋ፦ የዋንጫ ባለድሉ ባዬርን ሌቨርኩሰን አመርቂ ድል እየተደጋጋመ ነው ። ሁለት ተጨማሪ የዋንጫ ግጥሚያዎች ይጠብቁታል ። በሻምፒዮንስ ሊግ ደግሞ  የጀርመኑ ቦሩስያ ዶርትሙንድ እና የስፔኑ ሪያል ማድሪድ ዋንጫውን ለማንሳት ከሁለት ሳምንታት በኋላ በፍጻሜው ይፋለማሉ ።

አትሌቲክስ      

በዶሀ ዳይመን ሊግ በ3000 ሜትር መሠናከል በወንዶች ፉክክር እና በ1500 ሜትር የሴትቶች ሩጫ ውድድር ኢትዮጵያን አትሌቶች በሳምንቱ መጨረሻ ላይ አሸናፊ ሆነዋል ።  በ3000 ሜትር መሠናከል የወንዶች ፉክክር የግሉን ሰአት በማሻሻል ለድል የበቃው አትሌት ሳሙኤል ፍሬው ነው (8:07.25 1ኛ)። በዚህ ውድድር አትሌት ጌትነት ዋሌ (በ 8:09.69) 3ኛ ደረጃ አግኝቷል ።

በ1500 ሜትር ሴቶች ፉክክር ደግሞ አትሌት ፍሬወይኒ ኃይሉ (4:00.42) 1ኛ ወጥታለች ። ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ወርቅነሽ መሰለ(4:01.25) 4ኛ ደረጃ አግኝታ አጠናቃለች ። በ5000 ሜትር ሴቶች ሩጫም አትሌት እጅጋየሁ ታዬ (14:29.26) 2ኛ ስትወጣ፥ መዲና ኢሳ(14:34.11) የ3ኛ፤ መልክናት ውዱ (14:44.17) የ4ኛ ደረጃን አግኝተዋል ። በ800 ሜትር ሴቶች ፉክክር አትሌት ሀብታም ዓለሙ (1:59.08) 4ኛ ደረጃ አግኝታ አጠናቃለች ።

እግር ኳስ

የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን የሦስተኛ ዙር የመጀመራያ ጨዋታውን ከኬንያ ጋ ዐርብ በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም አድርጎ ያለምንም ግብ ተለያይቷል ። የመልሱ ጨዋታ የፊታችን እሁድ ኬንያ ውስጥ ይከናወናል። እስካሁን በተደረጉ ግጥሚያዎች፦ ጅቡቲ በቡሩንዲ ቡድን ትናንት የ18 ለ0 ብርቱ ሽንፈትን በማስተናገድ የግብ ጎተራ ሆናለች ። ትናንት በነበረ ሌላ ግጥሚያ ዛምቢያ ዩጋንዳን 2 ለ0 አሸንፋለች ። ቅዳሜ ዕለት፦ ሴኔጋል ላይቤሪያን 3 ለ1 ስታሸንፍ፤ ቡርኪናፋሶ እና ናይጄሪያ አንድ እኩል ተለያይተዋል ። ዐርብ ዕለት ከኢትዮጵያ እና ኬንያ ግጥሚያ በተጨማሪ በነበረ ጨዋታ፦ ሞሮኮ አልጄሪያን 4 ለ0 ረትታለች ። 

ከ17 ዓመት በታች የሴቶች የዓለም ዋንጫ የሚያልፉ ሃገራት የሚታወቁት ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ በሚከናወኑት አራተኛ ዙር ግጥሚያዎች ይሆናል ። የዘንድሮውን የዓለም ዋንጫ ከሕዳር መገባደጃ አንስቶ የምታስተናግደው የዶሚኒክ ሪፐብሊክ ናት ።

አዲስ አበባ ስታዲየም ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ዳግም መቼ ማስተናገድ ይጀምራል?
አዲስ አበባ ስታዲየም ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ዳግም መቼ ማስተናገድ ይጀምራል?ምስል Omna Tadel

ፕሬሚየር ሊግ

እንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ  ትናንት ማንቸስተር ዩናይትድን አንድ ለዜሮ ያሸነፈው አርሰናል አንድ የመጨረሻ ጨዋታ እየቀረው በ86 ነጥብ አንደኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች የሚቀሩት ማንቸስተር ሲቲ በአርሰናል የሚበለጠው በአንድ ነጥብ ብቻ ነው ። ማንቸስተር ሲቲ ነገ በቶትንሀም ሆትስፐር ስታዲየም ቶትንሀምን ካሸነፈ የመሪነቱን ስፍራ ከአርሰናል ይረከባል፥ በሁለት ነጥብ ልዩነትም ይበልጣል ማለት ነው ። አቻ ከወጣ በነጥብ ከአርሰናል ጋ ተስተካክሎ በግብ ክፍያ ግን የሁለተኛ ደረጃው ላይ ይቆያል ። ያም በመሆኑ የነገውን የማንቸስተር ሲቲ ግጥሚያ የአርሰናል ደጋፊዎች እጅግ በተለየ ሁናቴ ነው የሚከታተሉት ። ምናልባትም ማንቸስተር ሲቲ እንዲሸነፍ በመጸለይ ጭምር ።

የማንቸስተር ሲቲ አሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ ቶትንሀምን በሜዳው ለማሸነፍ «ለየት ያለ» ያሉትን «ነገር» እንደሚሞክሩ ዛሬ ተናግረዋል ።  ያ የተለየው ነገር ምን እንደሚሆንም በርካቶች በልዩ ትኩረት የሚጠብቁት ነው ። ቡድናቸው በቶትንሀም ሜዳ ከዚህ ቀደም ተጫውቶ «ግብ ማስቆጠርም ሆነ ማሸነፍ» እንዳልቻለ የተናገሩት ፔፕ ጓርዲዮላ፦ ነገ የተለየ ነገር ካላደረጉ ዋንጫው የአርሰናል ይሆናል ብለዋል ። እናስ አሰልጣኙ የተለየ ያሉት ነገር ሳይሳካ ቶትንሀም አርሰናል ይታደግ ይሆን?

አርሰናል አንድ ቀሪ 38ኛ ጨዋታውን የፊታችን እሁድ ከኤቨርተን ጋ ያደርጋል ። ማንቸስተር ሲቲ ደግሞ የመጨረሻ ግጥሚያውን በተመሳሳይ ቀን እና ሰአት የሚያደርገው ከዌስትሀም ዩናይትድ ጋ ነው ።

ዘንድሮ የፕሬሚየር ሊግ ዋንጫውን ማን ይወስደው ይሆን?
ዘንድሮ የፕሬሚየር ሊግ ዋንጫውን ማን ይወስደው ይሆን? ማንቸስተር ሲቲ ወይንስ አርሰናል?ምስል Dave Thompson/AP Photo/picture alliance

በሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሊቨርፑል ዛሬ ማታ ቪላ ፓርክ ስታዲየም ውስጥ አስቶን ቪላን ይገጥማል ፥ 38ኛ እና የመጨረሻ ጨዋታውን ደግሞ እሁድ ከዎልቭስ ጋ ያደርጋል ።  ሁለቱንም ቀሪ ጨዋታዎቹን ቢያሸንፍ እንኳ አሁን ማንቸስተር ሲቲ ካለው 85 ነጥብ በአንድ መበለጡ አይቀርም ።  ቀሪ ሁለት ጨዋታዎቹ የአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ  ቦታውን ላረጋገጠው ሊቨርፑል የሚፈይዱት ነገር የለም ።

ባይሆን 67 ነጥብ ሰብስቦ 4ኛ ደረጃ ላይ ለሚገኘው አስቶን ቪላ ቀሪ ሁለት ግጥሚያዎች የሞት ሽረት ናቸው ። የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ አራተኛ ቡድንነቱን በአስተማማኝ መልኩ ለማረጋገጥ ቀሪ ሁለት ጨዋታዎቹን ማሸነፍ ይጠበቅበታል ። ዛሬ ከሊቨርፑል ጋ ከሚያደርገው ግጥሚያ ባሻገር እሁድ ከክሪስታል ፓላስ ጋ ያለው ጨዋታንም ካላሸነፈ ቶትንሀም ሆትስፐር ያሰጋዋል ። ቶትንሀም በ63 ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። በዚሁ ካጠናቀቀ የአውሮጳ ሊግ የምድብ ተጋጣሚነቱን እንደተጠበቀ ይቆያል ። የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ ለመሆን ግን ቀሪ ሁለት ጨዋታዎቹን አሸንፎ የአስቶን ቪላን ሽንፈት አለያም አቻ መሆን መማጸን ይኖርበታል ።   ከሊቨርፑልም ሆነ ከክሪስታል ፓላስ ጋ ቀሪ ጨዋታዎቹን የሚያደርገው አስቶን ቪላ በሁለቱም ነጥብ ይጥላል ማለት ግን ይከብዳል ።

ቡንደስ ሊጋ

የጀርመን ቡንደስሊጋ የዘንድሮ ዋንጫን ቀደም ሲል መውሰዱን ያረጋገጠው ባዬርን ሌቨርኩሰን ትናንት ቦሁምን 5 ለ0 ድባቅ መትቶ አሸንፏል ። ባዬርን ሌቨርኩሰን ከሳምንት በፊትም አይንትራኅት ፍራንክፉርትን በቡንደስሊጋው ያደባየው 5 ለ1 ነበር ። በሚቀጥለው ሳምንት ቅዳሜ ከካይዘርስላውተርን ጋ የጀርመን እግር ኳስ ማኅበር (DFB) ፍጻሜ ይጠብቀዋል ። የፍጻሜ ተጋጣሚው ካይዘርስላውተርን በቡንደስሊጋ ሁለተኛ ዲቪዚዮን 15ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ቡድን ነው ። በሚቀጥለው ሳምንት ረቡዕ ደግሞ በአውሮጳ ሊግ የዋንጫ ፍልሚያ አታላንታ ይጠብቀዋል ።  ለበርካታ ዓመታት የቡንደስሊጋ ዋንጫን እየተቁለጨለጨ ዘንድሮ የተሳካለት ባዬርን ሌቨርኩሰን በዣቪ አሎንሶ የአሰልጣኝነት ዘመን ሦስት ዋንጫዎችን ሰብስቦ በርካቶችን ያስደምም ይሆን?

ከቡንደስሊጋው ዳርምሽታድት ወደ ታችኛው ዲቪዚዮን መውረዱን አረጋግጧል ። በአጠቃላይ ከ14ኛ እስከ 17ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት፦ ቦሁም፤ ማይንትስ፤ ዑኒዮን ቤርሊን እና ኮሎኝ የመውረድ እና የመዋዠቅ ሥጋት ገጥሟቸዋል ።

 ከታችኛው ዲቪዚዮን ሳንክት ፓውሊ እና ሆልሽታይን ኪል ቡድኖች
ከታችኛው ዲቪዚዮን ሳንክት ፓውሊ እና ሆልሽታይን ኪል ቡድኖች አንደኛ እና ሁለተኛ በመሆን ወደ ዋናው ቡንደስ ሊጋ ማለፋቸውን አረጋግጠዋልምስል Axel Heimken/dpa/picture alliance

17ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ኮሎኝ ቀጣዩን ግጥሚያ አሸንፎ ዑኒዮን ቤርሊን ከተሸነፈ ከቡንደስሊጋው ከመሰናበት ለጊዜው ይተርፋል። ሆኖም ከታችኛው ዲቪዚዮን ሦስተኛ ደረጃ ይዞ ካጠናቀቀው ፎርቱና ዱይስልዶርፍ ቡድን ጋ ተጋጥሞ በሚኖረው ውጤት ይሆናል በቡንደስሊጋው መቆየት አለያም መሰናበቱን ወደፊት የሚያረጋግጠው ።  በቡንደስሊጋው የዘንድሮ የመጨረሻ ግጥሚያ ቅዳሜ በሐይደንሀይም ከተሸነፈ አለያም ዑኒዮን ቤርሊን ፍራይቡርግን ማሸነፍ ከቻለ ግን ኮሎኝ ያበቃለታል ።  ኮሎኝ ወደ ቡንደስሊጋ ሁለተኛ ዲቪዚዮን መሰናበቱ አይቀርም ።የሚያዝያ 14 ቀን 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ከዑኒዮን ቤርሊን በሁለት ነጥብ በልጦ 15ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ማይንትስም በቡንደስሊጋው ለመቆየት ቮልፍስቡርግን ማሸነፍ ይጠበቅበታል ። አቻ ከወጣ ግን 30 ነጥብ ያለው ዑኒዮን ቤርሊንን ውጤትን ማየት አለበት ። 33 ነጥብ ያለው ቦሁም ራሱ ቬርደር ብሬመንን ማሸነፍ አለያም አቻ መውጣት ካልቻለ የሌሎቹን ውጤት ጠብቆ ሊዋዥቅም ይችላል ። ያም ማለት፦ ማይንትስ እና ዑኒዮን ቤርሊን ካሸነፉ ቦሁም በቡንደስሊጋው ለመቆየት ከታችኛው ዲቪዚዮን ሦስተኛ ደረጃ ይዞ ካጠናቀቀ ቡድን ጋ መጋጠም ግድ ሊሆንበት ነው ።

ቡንደስሊጋ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ውስጥ እነማን ቀልጠው ቀሩ?

በነገራችን ላይ ከታችኛው ዲቪዚዮን ሳንክት ፓውሊ እና ሆልሽታይን ኪል ቡድኖች አንደኛ እና ሁለተኛ በመሆን ወደ ዋናው ቡንደስ ሊጋ ማለፋቸውን አረጋግጠዋል ። በሁለተኛው ዲቪዚዮን እንደ ሐምቡርግ፤ ሻልከ፤ ኑይርንበርግ፤ ሔርታ ቤርሊን እና ሐኖቨር ያሉ የቀድሞ የቡንደስሊጋ ተፎካካሪ ቡድኖች ቀልጠው ቀርተዋል ።

ጀርመናውያንኑ ቶኒ ክሮስ እና ቶማስ ሙይለር፦ የሪያል ማድሪድ እና ባዬርን ሙይንሽን መለያን ለብሰው
ጀርመናውያንኑ ቶኒ ክሮስ እና ቶማስ ሙይለር፦ የሪያል ማድሪድ እና ባዬርን ሙይንሽን መለያን ለብሰው ምስል Christian Kolbert/kolbert-press/IMAGO

አይንትራኅት ፍራንክፉርት የቀጣይ የአውሮጳ ሊግ የምድብ ተጋጣሚነት ቦታውን ላለማጣት ቅዳሜ ዕለት ላይፕትሲሽን ማሸነፍ አለያም አቻ መውጣት ይጠበቅበታል ። ሆፈንሀይም በበኩሉ፦ የአይንትራኅት ፍራንክፉርትን ቦታ ለመውሰድ ወይንም የአውሮጳ ሊግ ኮንፈረንስ የማጣሪያ ተወዳዳሪነት ቦታውን በፍራይቡርግ ላለመነጠቅ ከባዬርን ሙይንሽን ጋ የሞት ሽረት ግጥሚያ ያደርጋል ። የቅዳሜው ግጥሚያ በአንጻሩ ለባዬርን ሙይንሽን የሚቀይረው ነገር የለም ። እንደ መሪው ባዬርን ሌቨርኩሰን፤ ሽቱትጋርት፤ ላይፕትሲሽ እና ቦሩስያ ዶርትሙንድ የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊነቱ እንደተጠበቀ ነው ። ይህም በመሆኑ ቅዳሜ የሚጠናቀቀው ቡንደስሊጋ ግጥሚያዎች በመውረድ እና በመዋዠቅ መካከል የሚደረጉ በመሆናቸው እጅግ አጓጊ ናቸው ። 

በሴቶች የጀርመን እግር ኳስ ፍጻሜ ቮልፍስቡርግ ባዬርን ሙይንሽንን አሸንፎ ዋንጫቻውን ለዐሥረኛ ጊዜ መውሰድ ችሏል ። ቮልፍስቡርግ ባዬርን ሙይንሽንን 2 ለ0 አሸንፎ ዋንጫውን የወሰደው ሐሙስ ዕለት ነው ። ትናንት በነበረው የቡንደስሊጋ የወንዶች ግጥሚያ በተቃራኒው ባዬርን ሙይንሽን ቮልፍስቡርግን 2 ለ0 አሸንፏል ። ተሰናባቹ ዳርምሽታድት ትናንት በሆፈንሀይም እንደማይሆን ሆኖ ተሸንፏል፥ 6 ለ0 ።

ኬሊያን ምባፔ

የፓሪ ሳንሳንጃርሞ አጥቂ ኬሊያን ምባፔ ወደ ስፔኑ ሪያል ማድሪድ ሊዛወር እንደሆነ እየተነገረ ነው ። ኬሊያን ምባፔ ባለፈው ዐርብ ከፓሪ ሳንጃርሞ እንደሚለቅቅ ካሳወቀ በኋላ ወደ የትኛው ቡድን እንደሚሄድ የታወቀ ነገር አልነበረም ። አሁን ግን ፈረንሣዊው አጥቂ ወደ ስፔኑ ሪያል ማድሪድ ማቅናቱ የማይቀር መሆኑ ተዘግቧል፥ የሚጠበቀው መቼ የሚለው ነው ።

የፓሪ ሳንሳንጃርሞ አጥቂ ኬሊያን ምባፔ ወደ ስፔኑ ሪያል ማድሪድ ሊዛወር እንደሆነ እየተነገረ ነው። ከማትስ ሁምል ኳስ ሊቀማ
የፓሪ ሳንሳንጃርሞ አጥቂ ኬሊያን ምባፔ ወደ ስፔኑ ሪያል ማድሪድ ሊዛወር እንደሆነ እየተነገረ ነው ። ቢጫ የለበሰው የቦሩስያ ዶርትሙንድ ተከላካይ ማትስ ሁመል ነው ምስል FRANCK FIFE/AFP

በፈረንሣይ ሊግ አንድ ፓሪ ሳንጃርሞ እሁድ ከቱሉዝ ጋ በተጫወተበት ወቅት የቡድኑ ደጋፊዎች ለኬሊያን ምባፔ አድናቆታቸውን ገልጠውለታል ። «ከፓሪስ ከተማ መዳረሻ ልጅነት የፓሪ ሳንጃርሞ ዝነኛው ወሳኝ ሰው ሆነሀል» ሲሉም አወድሰውታል ።  ያደነቁትን ያህልም ትናንት ጨዋታው ሲጀመር እና የኬሊያን ምባፔ ስም ሲጠራ በፉጨት ተቃውሟቸውን የገለጡም ነበሩ ። በትናንቱ ግጥሚያ ምንም እንኳን ኬሊያን ምባፔ ጨዋታው በተጀመረ በስምንተኛው ደቂቃ ላይ ብቸኛዋን ግብ ለፒኤስጂ ቢያስቆጥርም፥ ቱሉዝ ሦስት ለአንድ ማሸነፍ ችሏል ። 

በፈረንሣይ ሊግ በ70 ነጥብ እየመራ ዋንጫውን መውሰዱን ቀደም ሲል ያረጋገጠው ፓሪ ሳንጃርሞ፥ ባለፈው ሳምንት ከአውሮጳ ሻፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ መሰናበቱ ይታወሳል ። በግማሽ ፍጻሜ ውድድሩ የፈረንሣዩ ፓሪ ሳን ጃርሞን 1 ለ0 አሸንፎ በደርሶ መልስ የ2 ለ0 ውጤት ያሰናበተው የጀርመኑ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ነው ።

ቦሩስያ ዶርትሙንድ እንግሊዝ ዌብሌይ ስታዲየም ውስጥ ግንቦት 24 በሚካሄደው የፍጻሜ ውድድር የስፔኑ ሪያል ማድሪድን ይገጥማል ። ኬሊያን ምባፔን ሊወስድ ነው የተባለው ሪያል በሜዳው ሳንቲያጎ ቤርናቤዉ ባዬርን ሙይንሽንን ገጥሞ ሁለት ለአንድ በማሸነፍ ነው ለፍጻሜ የበቃው ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዲንሳ